10ኛው የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አመታዊ አገራዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በስኬት ተጠናቀቀ ፡፡

ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ 10ኛውን አመታዊ አገራዊ የምርምር ጉባኤውን እያካሄደ ሲሆን በምርምር ጉባኤው 60 ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርቡም ታውቋል ፡፡ ከጥናታዊ ጽሁፎቹ 30 የሚሆኑት የጉባኤው አዘጋጅ በሆነው ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ቀሪዎቹ 30 ጽሁፎች ደግሞ ከተለያዩ የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ ተመራማሪዎች በመቅረብ ላይ ይገኛል ፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ዶ/ር አብዮት አስረስ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ለጉባኤው ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት አመታት በርካታ ችግር ፈች የሆኑ የምርምር ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል ፡፡ ወደፊትም የማህበረሰባችንን ችግር የሚፈቱ ጥናቶችን ላይ ትኩረት በማድረግ ይሰራል ብለዋል ፡፡

የሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ በበኩላቸው በጉባኤውን በይፋ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በመማር ማስተማር፣ጥናትና ምርምርና እንዲሁም በማህበረሰብ አገልግሎት ያሳየውን አበረታች ለውጥ አውስተው በጥናትና ምርምር ዘርፍ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል ፡፡ወደፊትም የማህበረሰባችንን ችግሮች በዘላቂነት ሊፈቱ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ጥናት ማካሄዱን ይቀጥላል ብለው ለዚህ 10ኛው የጥናትና ምርምር ጉባኤ መሳካት አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን በተለይም ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህረት ሚኒስቴር እንዲሁም ከአገራችን አንጋፋ ዩኒቨርሲጭምር ጥሪያችንን አክብረው ለተገኙት ታዋቂ ተመራማሪዎች አድናቆታቸውን ገልጸዋል ፡፡
በጉባኤው በዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት በዶ/ር አብዮት አስረስ አማካኝነት ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ እስከዛሬ ያከናወናቸውን የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች በወፍ በረር ለጉባኤው ታዳሚዎች ቀርቧል ፡፡
Light of the Green Valley!
Mizan-Tepi University