ሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የመምህራንና ሠራተኞቹን ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የረጅም ጊዜ የብድር አገልግሎት ከኦሮሚያ ባንክ ጋር ተፈራረመ

(ሚቴዩ የካቲት 28/2014 ዓ/ም)፡- ሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የመምህራንና ሠራተኞቹን ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የረጅም ጊዜ የብድር አገልግሎት ከኦሮሚያ ባንክ ጋር ተፈራረመ፡፡

ዩኒቨርሲቲው መላውን መምህራንና ሠራተኞቹን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የረጅም ጊዜ ብድር አገልግሎት አስመልክቶ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ ሲገልጹ ከኦሮሚያ ባንክ ጋር ሌሎች ባንኮችም ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት መቅረባቸውን ገልጸው በኦሮሚያ ባንክ በኩል የቀረበው አማራጭ የተሻለ በመሆኑ ስምምነት መፈረሙን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አክለውም ሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ይህን ስምምነት መፈረሙ ለበርካታ አመታት በዩኒቨርሲቲው ሲስተዋል የነበረውን የሠራተኞች ፍልሰት በእጅጉ በመቀነስ በሥራው ቦታ ተረጋግተው እንዲኖሩ በማድረግ በኩል ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም ፕሬዚዳንቱ የዩኒቨርሲቲያችን ማህበረስብ የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን አቶ ተፈሪ መኮንን የኦሮሚያ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባል ያደረጉትን ድጋፍ አድንቀው በመላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስም አመስግነዋል፡፡አቶ እያዩ ኢሞ፤ የኦሮሚያ ባንክ ሚዛን-አማን ቅ/ሥ/አስኪያጅ በበኩላቸው ባንኩ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሲያደርግ ስምምነቱ ከተፈረመ ጊዜ ጀምሮ እንደባንኩ ሠራተኞችና የባንኩ ቤተሰብ አድርጎ እንደሚቆጥራቸውም ተናግረዋል፡፡ በብድር አገልግሎቱ ሠራተኛው ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ወይም ግዢ እንዲሁም መኪና ገዝቶ ለመጠቀም ቢፈልግ የብድሩ ተጠቃሚ እንደሚሆን ተናግረው የብድር ወለድ መጠኑንም አስመልክቶ አሁን ባንኩ ከሚያስከፈልገው የወለድ መጠን እንደራሱ ሠራተኞች ተመጣጣኝ ክፍያ እንደሚያስከፍልም አክለው ገልጸዋል፡፡በመጨረሻም ስምምነቱን ደ/ር አህመድ ሙስጠፋ፤ የሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት እንዲሁም አቶ እያዩ ኢሞ፤ የኦሮሚያ ባንክ ሚዛን-አማን ቅ/ሥ/አስኪያጅ፤ የዩኒቨርሲቲው ም/ፕሬዚዳንቶች በተገኙበት ተፈራርመዋል፡፡

Light of the Green Valley