ሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የክልልነት ምሥረታ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ዙሪያ ፓናል ውይይት አካሄደ።
ሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የክልልነት ምሥረታ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ዙሪያ ፓናል ውይይት አካሄደየሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ሰብአዊነት ኮሌጅ የክልልነት ምሥረታ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች በሚል ርዕሰ-ጉዳይ በቅርቡ በህዝበ-ውሳኔ ለማጽደቅ ዝግጅት በማድረግ ላይ ካለው ከደቡብ ምዕረብ ክልል 5 ዞኖችና ከአንድ ልዩ ወረዳ ከተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች ሰኔ 8/2013 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ፓናል ውይይት አካሄደ፡፡በውይይቱ መነሻ ላይ የሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሳይንስና ሰብአዊነት ኮሌጅ ዲን የሆኑት መ/ር ጎሳ አስናቀ ስለውይይቱ አጭር መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ቀጥሎም የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብዮት አስረስ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት እንዲሁም ፓናል ውይይቱ በአሁኑ ወቅት የሀገራዊ ምርጫና የደቡብ ምዕራብ ክልል ምሥረታ ህዝበ-ውሳኔ ጉዳይ የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ ምክንያት ዩኒቨርሲቲው ሂደቱ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ይካሄድ ዘንድ ታስቦ ፓናል ውይይት ማዘጋጀቱንና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮችን ካብራሩ በኋላ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ ፓናል ውይይቱን በንግግር ከፍተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ስለሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አመሰራረትና ሀገራዊ ተልዕኮውን በተለይም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል የነበሩ ተግዳሮቶችንና አሁን ላይ ሊተገበሩ ስለሚገባቸው ጉዳዮች በሰፊው አንስተው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አያይዘውም ይኸው ፓናል ውይይት የነበሩብንን ተግዳሮቶች ለመቅረፍና ለማጥራት ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ በመቀጠልም ከርዕሰ-ጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው 4 ጽሁፎች በዩኒቨርሲቲያችን መምህራንና ተመራማሪ በሆኑት በመ/ር እንዳለ ንጉሴ፤ መ/ር ዋሲሁን በዛብህ፤ መ/ር ፍቅሬ ዮሀንስ እና መ/ር አብለል ተከስተ በኩል በተከታታይ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በመጨረሻም የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች ሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለይም ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውይይቱን በማዘጋጀቱ የተሰማቸውን አድናቆት ገልጸው ዩኒቨርሲቲው በሌሎች አካባቢያዊ፤ ማህበራዊ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይበልጥ እንዲሰራ አስተያየት አቅርበዋል፡፡ ሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲLight of the Green valley